23/07/2026
የቁልቢ ገብርኤል በዓለ ንግስ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን ኮሚሽኑ አስታወቀ
በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል በዓለ ንግስ በሰላምና በደመቀ መልኩ እንዲከበር ለማስቻል የቅድመ ዝግጅቱን ተግባራት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነገራ ዱፌራ እንደገለጹት በዓሉ በሰላምና በደመቀ መልኩ እንዲከበር ለማስቻል ለሁሉም ፈፃሚ አመራር እና አባላት እንዲሁም አጋዥ ተቋማት የበዓሉን አከባበር የተመለከተ የፀጥታ እቅድ ወቶ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ከማድረግ ጀምሮ ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
አሁን ወቅትም የበዓሉ አከባበር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊ የሰው ኃይል ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶች እና ነዋሪው አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ወድያውኑ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ነገራ አያይዘውም ሊደርሱ የሚችሉ የትራፊክ አደጋዎች ለመከላከል መላ አሽከርካሪዎች በትእግስት እና የመንገድ አጠቃቀም ህግና ስርዓትን ባከበረ መልኩ ማሽከርከር ይገባቸዋል ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ባስተላለፉት መልዕክት ሰላም ወዳዱ የክልሉ ሕዝብ እንደ ወትሮው ሁሉ ከፖሊስና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ እንዲሰራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።