11/08/2026
"ለአደጋ ስጋት ምላሽ መስጠት የሚያስችል ተቋማዊ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ይገባል" :- አቶ ፍቅሬ አማን
ነሃሴ 05/2018 ዓ.ም (ቦንጋ ኤፍ ኤም 97.4) በክልሉ በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከተረጂነት ለመውጣት በየአከባቢው የሚከናወኑ ተግባራትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ በየዞኖች ድጋፋዊ ክትትል የሚያደርጉ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፣ ለአደጋ ስጋት ምላሽ መስጠት የሚያስችል ተቋማዊ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ብለዋል፡፡
የድጋፋዊ ክትትል ቡድኑ ጉድለቶችን መሙላት በሚያስችል መልኩ መከወን እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም የሚለው አስተሳሰብ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
አመራሩ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት መስራት አለበት ያሉት አቶ ነጋ፣ በተለይ የምግብ ክምችት፣ የመጋዘን ዝግጅት እና የግብርና ሥራዎች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በመድረኩ በሰጡት አስተያየት በክልሉ በቂ የምግብ ክምችት ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡
የሚከማቹ ምግቦች ደግሞ በተገቢው መንገድ በተዘጋጁ መጋዘኖች መቀመጥ እንዳለባቸው ገልጸው፣ ሁሉም ወረዳዎች ለዚሁ ተግባር የተዘጋጁ መጋዘኖች ሊኖሩ ይገባልም ብለዋል፡፡
ለቅፀበታዊ አደጋዎች የሚሆን የምግብ፣ የውሃ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ከወዲሁ በበቂ ሁኔታ እንዲዘጋጁ በተቋማት በጀት መያዝ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
ሁሉም ዜጎች ለአደጋ ስጋት መከላከል አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡