11/07/2026
ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግ/ማህበር (ማማ ወተት) ከጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት (GIZ) ጋር በመተባበር ላለፉት ሁለት ዓመታት በጋራ ሲያከናውን የቆየውን የ200 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት በተሳካ ሁኔታ አጠናቋል። ይህንን ተንተርሶ ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም በሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ቅጥር ግቢ በሚገኘው አዳራሽ ደማቅ የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል። በዕለቱም በፕሮጀክቱ አማካኝነት ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ልዩ ልዩ ዘመናዊ መሣሪያዎች ለወተት አምራች ህብረት ሥራ ማህበራት ተረክበዋል።
በዕለቱ በተካሄደው መርሃ-ግብር ላይ የድርጅቶቹ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ የልማት አጋሮች፣ የህብረት ሥራ ማህበራት አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። የሥነ-ሥርዓቱ ተሳታፊዎች ከፍተኛ አመራሮች ንግግር ካደመጡ በኋላ፣ ለወተት ማህበራቱ የተዘጋጁትን ዘመናዊ ቁሳቁሶችና መሣሪያዎች የጎበኙ ሲሆን፣ መርሃ-ግብሩ በምሳ ግብዣ ተጠናቋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወነው ታላቅ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የወተት እሴት ሰንሰለት ይበልጥ ለማጠናከር እና በአካባቢው የሚገኙ የወተት አቅራቢዎችን ኑሮ ለማሻሻል ያለመ ሲሆን፣ የሚከተሉትን ዋና ዋና ስኬቶች አስመዝግቧል፦
ዘላቂ የአቅርቦት መስመር መዘርጋት፦ ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ በቀን እስከ 40,000 ሊትር ጥሬ ወተት ከአካባቢው አምራቾች በቀጥታ ለመሰብሰብ የሚያስችለውን አስተማማኝና ዘላቂ የአቅርቦት ትስስር መረብ መዘርጋት ችሏል።
የእሴት ሰንሰለት እና የምግብ ዋስትናን ማጠናከር፦ የወተት አቅራቢዎችን የምርት ጥራትና መጠን በማሳደግ ገቢያቸውን ማሻሻል የተቻለ ሲሆን፣ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን ማሳደግ፦ ፕሮጀክቱ በመንግሥት ተቋማት፣ በግል ኢንተርፕራይዞች እና በዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች መካከል ያለውን ጠንካራ የሥራ ትብብር በተግባር ያሳየ ታላቅ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ ስኬት ማማ ወተት በኢትዮጵያ የወተት ማቀነባበሪያ ዘርፍ ያለውን ግንባር ቀደም ሚና ይበልጥ የሚያጠናክር ሲሆን፣ ለአካባቢው አምራቾች ሁለንተናዊ እድገት መፋጠንና ለተጠቃሚዎች ደግሞ ጥራታቸውን የጠበቁ የወተት ምርቶችን በስፋት ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየ ነው።
ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ለዚህ ታላቅ ፕሮጀክት መሳካት አብረዋቸው ለሠሩት ለGIZ፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ ለህብረት ሥራ ማህበራት እና ለውድ የወተት አቅራቢ አጋሮቹ በሙሉ የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል።