25/07/2026
በቅድመ ጎርፍ መካከል ስራ ከ229 ሺህ በላይ ሰዎችን ከመፈናቀል ማዳን ተችሏል
+++++++++++
በጎርፍ ተጋላጭነታቸው ቅድሚያ በተሰጣቸው አካባቢዎች በተሰራው የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ ከ229 ሽህ በላይ ሰዎችን ከመፈናቀል ማዳን መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከተጠሪ ተቋማትና ከክልሎች ውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች ጋር የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ይገኛል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት፤ በጎርፍ ተጋላጭነታቸው ቅድሚያ በተሰጣቸው ተፋሰሶች አካባቢ 255 ነጥብ 65 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ሥራ ተሰርቷል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ይከሰት የነበረው የጎርፍ አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል።
የጎርፍ መከላከል ሂደቱ በአዋሽ ተፋሰስና በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች አካባቢ የተተገበሩ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህም 70 ሺህ 140 ሄክታር የእርሻ ማሳና 229 ሺህ 189 ሰዎችን ከመፈናቀልና ከጉዳት መከላከል መቻሉን ጠቁመዋል።
በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ቅንጅታዊ አሰራር እውን ማድረግ መቻሉን በመግለጽ፤ በክልሎች መካከል ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ የተደራሽነት ልዩነት ለማጥበብ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
በሀገሪቱ አጠቃላይ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን 75 ነጥብ 59 በመቶ ደርሷል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የገጠርና ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግ በትኩረት መሰራቱንም አብራርተዋል፡፡
በዚህም አጠቃላይ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር ከ84 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡