23/07/2026
በሀረሪ ክልል ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ነፃ የጤና ምርመራና ህክምና እየተሰጠ መሆኑ ተገለጸ
በሀረሪ ክልል ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ነፃ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አካል የሆነው ነፃ የህክምና አገልግሎት "በጎነት ለጤናማ ማህበረሰብ" በሚል ሀሳብ ነው እየተሰጠ የሚገኝው።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አብዲ አሚን እንደገለጹት እየተሰጠ የሚገኝው ነፃ የምርመራና የህክምና አገልግሎት አቅመ ደካማ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
ነፃ የህክምና አገልግሎቱ በበጎ ፍቃደኛ የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው አገልግሎቱም በመንግስትና በተመረጡ የግል ጤና ተቋማት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
እየተሰጡ ከሚገኙ የጤና ምርመራዎች መካከልም የስኳር ህመም፣ የደም ግፊት፣ ከአንገት በላይ፣ የቆዳና የአይን እና የልብ ሕመም ምርመራና ሕክምና እንዲሁም ሌሎች ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ይገኙበታል ብለዋል ከዚህ በተጨማሪም ከ5 ሺህ በላይ የደም ልገሳ መርሃ ግብሮች እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በምርመራው ወቅትም ተጨማሪ ህክምና ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ወደ ሚመለከታቸው የጤና ተቋማት በመላክ አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ከዚህ በተጨማሪም በዘመቻው ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስመልክቶ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ዘመቻው የጤና አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የህዝብን የጤና ንቃት ለማሳደግና የመረዳዳት ባህልን ለማሳደግ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ይህንን በመገንዘብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።