08/13/2026
እስከ 50 ሺህ ብር ቅጣት፤ በአዲስ አበባ የመስተንግዶ ሰራተኞች አለባበስ ላይ የወጣው አዲሱ ደንብ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ ገባ!
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ባሮች፣ ሬስቶራንቶች እና ሆቴሎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሴት የመስተንግዶ ሰራተኞችን አለባበስና ጌጣጌጥ አጠቃቀም የሚደነግገው ሕግ በሙሉ አቅሙ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተነገረ።
ደንቡን በማያከብሩ የመስተንግዶ ተቋማት ላይ እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ተጨማሪ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተመልሷል።
አዲሱ ደንብ ቁጥር 178/2017 በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ጥብቅ ክልከላ ጥሏል፡
1. ከጉልበት በላይ የሆኑ አጫጭር ቀሚሶችን መልበስ፣
2. የደረት ክፍልን ክፍት የሚያደርጉ አልባሳትን መጠቀም፣
3. ከጋብቻ ቀለበት ውጪ ባሉ በሚታዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ የሚደረጉ ማናቸውንም ጌጣጌጦች ማድረግ።
የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር መስራችና ሥራ አስፈጻሚ አባል ናፍቆት ጌታሁን ከአሐዱ ሬድዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ የተወሰኑ መለያ ልብሶች (ዩኒፎርሞች) ከማህበረሰቡ ባህልና እሴት ያፈነገጡ ነበሩ።
ይህንን አሰራር ለማስተካከል ማኅበሩ ከአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን እና ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ደንቡ እንዲጸድቅና ወደ ትግበራ እንዲገባ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በመስተንግዶ ተቋማት የሚለበሱ መለያ ልብሶች ጨዋነትንና ሙያዊ ብቃትን ያማከሉ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል።
ማኅበሩም የመንግስትን ክትትል በመደገፍ የአፈጻጸም ቁጥጥር እያደረገ እንደሆነና፣ ደንቡን በማያከብሩ አካላት ላይ ለቱሪዝም ኮሚሽኑ ሪፖርት የሚያደርግ ቢሆንም እስካሁን የቀረበ ጥሰት አለመኖሩ ተገልጻል።
Via አሐዱ ሬድዮ